ዲያቆን ሄኖክ ሃይለ
++ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? ++ ዘፍ. 4፡9 ቃየን እና አቤል የምድራችን የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ከእነርሱ በፊት የነበረው ወንድ አባታቸው አዳም ነው፡፡ አዳም ደግሞ ከአፈር በመገኘትዋ እኅቱ ፣ ከጎኑ በመውጣትዋ ልጁ ፣ ረዳት እንድትሆነው በመሠጠትዋ ደግሞ ሚስቱ የሆነችው ሔዋን አብራው ከመሆንዋ በስተቀር አብሮት የሚሆን ወንድም አልነበረውም፡፡ ቃየን እና አቤል ግን የወንድማማችነት ጸጋ የመጀመሪያዎቹ ተካፋዮች ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ወንድማማቾች እንግዳ የሆነ ሰው ኖሮ ለማስተዋወቅ አንሞክርም፡፡
ታሪካቸው በበጎም ሆነ በክፉ ገጽታው ሲተረክ የኖረ ነው፡፡ ሆኖም ከሰባት ሺህ በላይ ዓመታት በኋላ የቃየኖችና የአቤሎች ቁጥር እጅግ በበዛበት ዘመን ላይ ሆነን ስለዚህ ታሪክ ማስታወስ ዛሬን በትናንት መስታወትነት ለመመልከት እና እኛም በጠባያችን ከሁለቱ ወንድማማቾች ማነኛቸውን እንደምንመስል ለማየት ይረዳናል፡፡ † የወንድማማቾቹ መሥዋዕት † አቤል እረኛ ሲሆን ቃየን ደግሞ ገበሬ ነበር፡፡ ሁለቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ሊያቀርቡ ተነሡ፡፡ እረኛው አቤል ‹ከበጎቹ በኲራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ ገበሬው ቃየን ደግሞ ከምድር ፍሬ አቀረበ፡፡ ለእግዚአብሔር ‹መሥዋዕትን ማቅረብ› ከዚያ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ይህ የወንድማማቾቹ ሥራ ከአባታቸው ከአዳም የተቀበሉት ትውፊት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡ እግዚአብሔር ለምን የቃየንን መሥዋዕት አልተቀበለውም? ለምንስ የአቤልን ተቀበለው? የአቤል መሥዋዕት በግ ስለሆነ የቃየን ደግሞ እህል ስለ ሆነ ይሆን? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ሁለቱም ያቀረቡት እንደየውሎአቸውና እንደየሙያቸው ነው፡፡ እረኛው አቤል እንዳዋዋሉ ከበጎቹ መሥዋዕት ሲያቀርብ ገበሬው ቃየን ደግሞ እንደ አዋዋሉ የምድርን ፍሬ አቀረበ፡፡ ታዲያ ምንድር ነው ችግሩ? በዚያ ላይ ለእግዚአብሔር ከእህል ወገን ቊርባንን ከእንስሳ ወገን ደግሞ መሥዋዕትን ማቅረብ በብሉይ ኪዳን ለሰዎች የተፈቀዱ ሁለት አማራጮች ነበሩ፡፡ እንዲህ ከሆነ ታዲያ እግዚአብሔር ለምን የቃየንን መሥዋዕት አልተቀበለለትም?? እግዚአብሔር አስቀድሞ የተመለከተው የቀረበለትን መሥዋዕት ሳይሆን የአቅራቢዎቹን ልብ ነበር፡፡ አቤል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሲያቀርብ በንጹሕ ልቦና እና በፍርሃት እንደነበረ መሥዋዕቱን ለማቅረብ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት ያሳያል፡፡ ‹‹ከበጎቹ በኲራት እና ከስቡ አቀረበ›› ነው የሚለው፡፡ ከበጎቹ መካከል በኩራቱን መርጦ ከሥጋውም ደግሞ ስቡን መርጦ ተጨንቆ ነበር ያቀረበው፡፡ ቃየን ግን በግዴለሽነትና በትዕቢት የተሞላ ነበር፡፡ የምድርን ፍሬ ሲያቀርብም ያለ ምንም ጥንቃቄ ግርዱን አግበስብሶ አቀረበ፡፡ ለማቅረብ የተዘጋጀ አለመሆኑ ለፈጣሪው ያለውን ንቀት ያሳያል፡፡ ይህን በትዕቢት የተሞላ ልብ ይዞ ደግሞ እንኳን የምድርን ፍሬ የአቤልን ዓይነት ስብ ቢያቀርብም ኖሮ እንኳን እግዚአብሔር አይቀበለውም ነበር፡፡ አምላክ ‹እንደ ልቤ› ብሎ የጠራው ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን የልብ ፍላጎት እንዲህ ሲል ተናገረ ‹‹መሥዋዕትን ብትወድስ በሠጠሁህ ነበር ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም፡፡ የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፡፡ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም፡፡›› መዝ. ፶፥፲፮-፲፯ እግዚአብሔር ከሥጦታ ቀድሞ ሠጪውን ያያል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ›› የሚለው፡፡ ከመሥዋዕቱ በፊት የአቤልን ቅን ልብ አየው፡፡ መሥዋዕቱንም ተቀበለው፡፡ አቤል በዚህ ቅን ልቡናው ሆኖ የሚያቀርበው መሥዋዕት ባይኖረው እንኳን የተሰበረውን መንፈሱን መሥዋዕት አድርጎ ይቀበለው ነበር፡፡ የአቤል ዓይነት ልብ ያለው ሰው የሚያቀርበው መሥዋዕት ላይኖረው ይችላል፡፡ ‹‹ቢኖረኝ ኖሮ ለእግዚአብሔር ይህንን አቀርብ ነበር›› የሚል ብዙ ሰው አለ፡፡ ከዚህ ሰው ላይ እግዚአብሔር የማድረግ ሃሳቡን ብቻ ተቀብሎ መንግሥተ ሰማያትን ይሠጠዋል፡፡ ‹‹ሊሠጡ ወደው ሳሉ የሚሠጡት ከሌላቸው ላይ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ መንግሥተ ሰማያትን ይሠጣቸው ዘንድ›› ይላል ቅዳሴያችን፡፡ (ጸሎተ መባዕ ዘሐዋርያት) ቃየን ግን ሠጥቶ እንኳን እንዳይቆጠርለት ይህ በጎ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ ራሱን ሳይሠጥ መሥዋዕትን ሠጠ፡፡ ከፈረሱ ጋሪውን አስቀደመ፡፡ ሰብአ ሰገል ሥጦታ ይዘው ከሩቅ ሀገር ሲመጡ ወደ ቤተ ልሔም ሲመጡ ለጌታ ያቀረቡለት የመጀመሪያው ሥጦታ ምን ነበር? እንዲህ ነው የሚለው ‹‹ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ፣ ወድቀውም ሰገዱለት ፤ ሣጥናቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት›› (ማቴ. ፩፥፲፩) የመጀመሪያ ሥጦታቸው ስግደት ነበር፡፡ ሣጥን ከመክፈት በፊት ልብን መክፈት ይቀድማል፡፡ ልብን ሳይከፍቱ ሣጥንን ከፍተው የሚያቀርቡት ሥጦታ ግን እንደ ቃየን መሥዋዕት በከንቱ ይቀራል፡፡ ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? ‹‹ቃየን እጅግ ተናደደ ፤ ፊቱም ጠቆረ!›› ግን ምን አናደደው? ልብ አድርጉ ተናደደ ብቻ አይደለም ‹‹እጅግ ተናደደ›› ነው የሚለው፡፡ እንዲህ ፊቱን በቅጽበት ያከሰለውስ ምንድር ነው? ‹‹ለምን ፈጣሪዬ አልተቀበለኝም?›› ብሎ ይሆን? ‹‹አምላኬን ደስ ሳላሰኘው ቀረሁ›› ብሎ ተጸጽቶ ይሆን? አይደለም!! ስለ አምላኩ ደስታ የሚገደው ዓይነት ሰው ቢሆን ኖሮ ቀድሞውኑ መሥዋዕቱን በፍርሃት ባቀረበ ነበር፡፡ ቃየንን ምን እንዳቃጠለው ፣ አንጀቱም በምን እንዳረረ ለማወቅ በኋላ የፈጸመውን ድርጊት መመልከት ይበቃል፡፡ ቃየን የተናደደው የእሱ መሥዋዕት ተቀባይነት ስላላገኘ ሳይሆን የአቤል መሥዋዕት ተቀባይነት ስላገኘ ነው፡፡ ከራሱ ውድቀት ይልቅ የአቤል ስኬት አንገበበገበው፡፡ አዬ ቃየን! ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ እኮ ውድድር አይደለም፡፡ በውድድር ሥፍራ አንዱ ያቀረበው ነገር ከሌላው በልጦ ሲገኝ በመበለጡ ምክንያት የአንደኛው ወገን ውጤት ይቀንሳል፡፡ በመበለጡ ደረጃውን ያጣው ሰው ቢበሳጭ ብስጭቱ ምክንያታዊ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማገልገል ግን ውድድር አይደለም፡፡ አምላክም ‹‹ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን›› የሚከፍል ገዥ ነው፡፡ ብዙ ተጋድሎ ሲፈጽሙ የኖሩ ቅዱሳን የሚወርስዋትን መንግሥተ ሰማያት እንደ ቀኙ ወንበዴ ባለቀ ሰዓት ንስሐ የገቡ ሰዎችም የሚወርስዋት እግዚአብሔር ሁሉን ለየብቻው የሚመዝን አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ የቃየንና አቤልን መሥዋዕትም ሲመለከት ‹‹እስቲ ከሁለታችሁ ማን የተሻለ ነገር ማቅረብ ይችላል›› በሚል ማወዳደር አልነበረም፡፡ ወይም ከሁለቱ የአንዳቸውን ብቻ ሊመርጥ አልመጣም፡፡ የአንዱ መሥዋዕት በሌላው መሥዋዕት ላይ የሚፈጥረው አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አልነበረም፡፡ ዕድሉ
ለሁለቱም እኩል የተከፈተ ነበረ፡፡ ራሱ ባለቤቱም እንዲህ ብሎአል ‹‹ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? ፤ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚያበራ አልነበረምን?›› ነበር ያለው፡፡ ‹‹አንተም በቅን ልብ ሆነህ መሥዋዕት ብታቀርብልኝ ኖሮ የአንተንስ መሥዋዕት እቀበልህ አልነበረም? ፊት በመጥቆር ፈንታ ያበራ አልነበር?›› ሲል ነው፡፡ † ቃየን አቤልን ገደለው! ‹‹ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።›› ቃየን በወንድሙ ላይ ተነሣበት፡፡ ‹‹ለቅናት የለው ጽናት›› እንዲሉ ከወንድማዊ ፍቅር በላይ ቅናት ልቡን አሸንፎት ወንድሙን ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ ከሰው ልጆችም የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ሆነ፡፡ አቤልም የመጀመሪያው ሟች! አዳምና ሔዋንም ‹‹ልጄ ልጄ›› ብለው ለማልቀስ የመጀመሪያ ሆኑ፡፡ በእርግጥም የቃየን በደል ነፍስ ማጥፋት ብቻ አልነበረም፡፡ ጥፋቱን የሚያጎሉ ፣ ጨካኝ ነው የሚያስብሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ቃየን ለአቤል ታላቅ ወንድሙ ነው ፤ አቤል ደግሞ ታናሹ፡፡ ታላቅ ወንድም ሥራው ታናሹን መጠበቅ ፣ መንከባከብ ፣ ሌሎች እንዳይነኩት ተገን መሆን ነው፡፡ ‹‹ወንድምና ወጥ ማስፈራሪያ ነው›› ብለን ለምንተርት ለእኛ መቼስ ይኼ አይጠፋንም፡፡ ቃየን ግን ለአቤል ማስፈራሪያ አልሆነውም ፤ አስፈሪ ሆነበት እንጂ! ‹ወንድም ጋሻዬ› የሚለው ወንድሙ ጦር ሆኖ ተነሣበት፡፡ ከጠላት ሊጠብቀው ሲገባ ጠላት ሆነው፡፡ ከሞት አልከለለውም ፤ ይልቅ ራሱ ገደለው፡፡ አቤል የዋህና ታዛዥ ልጅ ነበር፡፡ ልቡ እንኳንስ በሰው ዘንድ ውስጥን በሚመረምር በእግዚአብሔር ዘንድም መልካም ነበረ፡፡ ቃየን ‹‹ና ወደ ሜዳ እንሒድ›› ሲለው ‹‹ለምንድር ነው የምንሔደው? ወደ የትኛው ሜዳ? /ዘመኑ ሜዳ የሞላበት ነውና/ ምን እንሠራለን?››› እንኳን ብሎ አልጠየቀውም፡፡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ ቃየን የቀናው በአቤል እንደመሆኑ አንዱ የአንዱን የስሜት መለዋወጥ ሊያዩ የሚችሉበት ዕድል ነበረ፡፡ የቃየን ፊት ሲጠቁር አቤል አይቷል፡፡ አሁን እንሒድ ሲለው ግን እንደሚጠላው እያወቀ ተከትሎት ሔደ፡፡ ‹‹እስመ ነፍስ ተአምር ቀታሊሃ›› (ነፍስ ገዳይዋን ታውቃለች) እንዲሉ አበው በክፉ የሚያየው ወንድሙን አምኖ ተከተለው፡፡ ምንም ምን ሳያይበት አምኖ ቢከተል ኖሮ እንደሞኝ በተቆጠረ ነበር፡፡ አቤል ግን የወንድሙን ጥላቻ ሲያውቅ አመኔታው ያልቀነሰ የዋህና ጻድቅ ነበር፡፡ በተለይም ሰው ጥላውን እንኳን በማያምንበት ዘመን ላይ ቁጭ ብለን ስናስታውሰው ጻድቁን አቤል የበለጠ እናከብረዋለን፡፡ መግደል ጨካኝነት ነው፡፡ እንደ ቃየን ያለ ታዛዥ እና የዋህን መግደል ደግሞ ምንኛ ይብስ ይሆን? ይህን ዓይነቱን ልጅ በድንጋይ ቀጥቅጦ መግደልስ እንዴት ዓይነት ጭካኔ ነው? ስለ አሟሟቱ የተጻፈው ‹ተነሣበት ገደለውም› የሚል ብቻ ነው፡፡ ቃየንና አቤል ታገሉ የሚል የለም፡፡ የዋሁ አቤል ምንም ሳይጠራጠር ራሱን ለመከላከል ሳይጠነቀቅ የሚሔድ ነበር ማለት ነው፡፡ በአቤል ሞት አዳምና ሔዋን ትንሹ ወንድ ልጃቸውን አጡ ፣ የዓለም የመጀመሪያው እረኛ ሞተ ፣ ሉድ ባልዋን አጣች፡፡ ቃየን ብቻ ነው ወንድሜን አጣሁ ቢል የማያምርበት፡፡ አቤል ከእናቱ ፣ ከአባቱ ፣ ከሚስቱ ተለየ፡፡ ገና ከተፈጠረች ብዙ ባልቆየች በሰው ብዛት ባላደፈች አዲስ ምድር ላይ የመኖሩን ተስፋ ነጠቀው፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ቃየን በአቤል ላይ የፈጸመው መግደል ብቻ አይደለም ፤ የዋህ ወንድሙን ብቻውን ወደ ሲኦል እንዲወርድ አድርጎታል፡፡ አቤል የተገደለበት ዘመን ጻድቃንም ጭምር ወደ ሲኦል የሚወርዱበት ፣ ‹ጽድቅ እንደ መርገም ጨርቅ› የሆነበት ዘመነ ፍዳ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ የአቤል ነፍስ ወደ ሲኦል ለብቻዋ ወርዳለች፡፡ ዲያቢሎስ በታሰረበት ሲኦል ለብቻ መሆን ምንኛ ከባድ ነው፡፡ ነገሩን አልን እንጂ ጻድቃን በሲኦል ሳሉ እንኳን ‹ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል› በተባለለት በእግዚአብሔር ረድኤት ይከለላሉ፡፡ ‹‹ነፍሶሙሰ ለጻድቃን ውስተ ዕደ እግዚአብሔር ወኢለከፎሙ ሥቃይ›› (የጻድቃን ነፍስ በእግዚአብሔር እጅ ነው ፤ ሥቃይም አላገኛቸውም) እንደሚል አቤል እንደርሱ ጻድቅ ሳሉ ወደ ሲኦል ከሚወርዱ ቅዱሳን ሁሉ ጋር ‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም›› ብሎ ያመሰግናል፡፡ (ኢሳ. ፵፥፲፩ ፣ መዝ. ፳፪፥፬ ፤ መጽሐፈ ጥበብ) ቃየን እና አቤል በነበሩበት ዘመን የዓለም ሕዝብ ቊጥር ስድስት ብቻ ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን ፣ አቤልና ቃየን ፣ ሉድና አቅሌማ፡፡ የሰው ዘር ዋጋ ምንኛ ውድ ነበር? እርግጥ ነው መቼም ቢሆን ሰው አይረክስም፡፡ ሁሌም ውድ ነው፡፡ እንዲያውም በሐዲስ ኪዳን የሰው ልጅ ዋጋ እጅግ ተወድዷል፡፡ በደመ ክርስቶስ ዋጋ ተገዝተን ከብረናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በነአቤል እና ቃየን ዘመን ከነበረው በጣት የሚቆጠር ሰው አንጻር የአንድ ሰው መሞት እጅግ ትልቅ ኪሳራ ነበር፡፡ ቃየን አቤልን ሲገድል እኮ የገደለው የዓለምን ሕዝብ አንድ ስድስተኛ ነበረ፡፡ አስቡት እንግዲህ! የዓለም ሕዝብ አንድ ስድስተኛ ማለት ዛሬ ሲተረጎም ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ ማለት ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) ይሏል ይኼንን ነው፡፡ ቃየን ‹‹አቤልን የገደልኩት ሳላስበው በድንገት በንዴት ተገፋፍቼ ነው›› ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህን ኃጢአት ሊፈጽም እንደሚችል ፣ ንዴቱን እንዲገታ ፣ ራሱን እንዲገዛ በወቅቱ የነበረው የሕግ አካል ፈጣሬ ዓለማት ፣ ሐጋጌ ሕግጋት እግዚአብሔር አስጠንቅቆት ነበር፡፡ ‹‹መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።›› ብሎታል፡፡ ግድያውን ከመፈጸሙ በፊት ማስጠንቀቂያ የተሠጠው ሰው ወንጀል ፈጽሞ ሲገኝ ምን ይባላል? የሕግ ሰዎች ይህን እንዴት ይተነትኑት ይሆን? የቃየን በደል መች አበቃና! ወንድሙን ገድሎት ሲመለስ እግዚአብሔር ጠየቀው፡፡ ‹ወንድምህ አቤል ወዴት ነው› ሲል፡፡ እርሱም አለ ‹አላውቅም ፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?› የእግዚአብሔር ጥያቄ መረጃን ፍለጋ አልነበረም፡፡ ቃየንን ገና ክፉ ሲያስብ አውቆታል፡፡ ‹ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?› የሚለው ጥያቄ ‹ወንድምህን ወዴት ጣልኸው? ወዴት አደረስኸው? እንዴት ጨከንክበት?› የሚል ቃየን ኃጢአቱን እንዲናዘዝ የቀረበለት ጥሪ ነበር፡፡ የሚካሰስለት ለሌለው አቤል እግዚአብሔር ራሱ ከሳሽ ሆኖ ተነሣ፡፡ ቃየን ግን ‹አላውቅም› አለ፡፡ እንኳን ለእግዚአብሔር ለሰው እንኳን የሚያውቁትን ‹አላውቅም› ብሎ መካድ እንዴት ከባድ ነው? ሰውንስ ማታለል ይቻላል፡፡ ሁሉ በእጁ ለተያዘ ፣ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ለማይጨልም አምላክ መዋሸት ምንኛ ከባድ ነው? ወንጀለኛው ቃየን ወንጀሉን ካደ፡፡ ከመግደሉ መካዱ ደግሞ የከፋ ሆነ፡፡ ቃየን አላቆመም ‹የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?› ብሎ በፈጣሪ ፊት አንደበቱን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ እግዚአብሔር ከቃየን ክህደት በላይ የሚጮኸውን የአቤልን ደም ድምፅ ሰማ ፤ ቃየንንም ረገመው፡፡ ቃየን ይኼን ጊዜ ያልተናዘዛትን ኃጢአቱን ‹ልሸከማት የማልችላት ናት› አለ፡፡ ኃጢአቴ ከበደኝ ማለት ንስሐ አይደለም ፣ ሸክምን ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ ቃየን ኃጢአት የሚፈጥረው ሥጋት አደረበት ‹‹ተቅበዝባዥ እሆናለሁ ያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል›› አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን ‹‹ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት›› ይላል፡፡ ዛሬ ወንጀል የፈጸመ ሰው ወንጀለኛም ቢሆን ታራሚ ሆኖ የመቆየት መብት አለው ፣ እንደ ዕባብ ተቀጥቅጦ ይሙት አይባልም፡፡ የወንጀለኛን መብት ማክበር እንደሚገባ የርኅራኄ ምንጭ የሆነው አምላክ የቃየንን መብት በመጠበቅ እና ከለላ በማድረግ አስተማረን፡ ወንድሞቻችን አቤሎች ወዴት ናቸው? አብረውን የቆሙ ፣ አብረውን መሥዋዕት ያቀረቡ ፣ ምናልባትም መሥዋዕታቸው ከእኛ ይልቅ ሊሠምር ፣ ብዙ ተስፋ የነበራቸው ብዙ ወንድሞቻችንን የት ጣልናቸው ይሆን? እግዚአብሔር በእርግጥ የማይጠይቀን ይመስላችኋል? ‹ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? ወዴት ጥለኸው መጣህ?› መባላችን የግድ ነው፡፡ ያን ጊዜ እንደ ቃየን ‹ጠባቂው እኔ ነኝን?› ብለን ራሳችን ነጻ እናደርግ ይሆን? በእርግጥ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ የአቤልን ደም ከቃየን እጅ የፈለገ አምላክ የወገኖቻችንን ጉዳይ እኛን መጠየቁ አይቀርም፡፡ ‹‹እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።›› ይለናል፡፡ (ሕዝ. ፫፥፲፰) እናም ባለ ዕዳዎች እንዳንሆን ፣ ሌሎች ቃየኖች እንዳንሆን አቤሎቻችንን ከያሉበት እንመልከት ፣ በቃየን ዓይን የምናየው ፣ የምንዝትበት ፣ የምንቀናበት ሰው ካለ በደጃችን የምታደባው ኃጢአት ላይ እንንገሥባት፡፡ ከክፋት ርቀን ወደ የዋህት በመቅረብ አቤልን እንምሰለው፡፡ ‹በወንድማማችም መዋደድ› ፍቅርን እንጨምር፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእስራኤል ነገድ በዘር ተከፍለው ሁለቱ ተለይተው ሲገነጠሉ በትንቢት አይቶ እያዘነ ፣ መከፋፈላቸው ለዘራቸው መጥፋት ምክንያት መሆኑን ተገንዝቦ የጸለየው ጸሎት ይህ ነበር "ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው!› ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ 2004 ዓ.ም ተጻፈ ከሞት ባሻገር ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment